በበጀት ዓመቱ ከ1 ሺ 391 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ግንባታና ጥገና ስራ ተከናውኗል
ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2017 በጀት ዓመት 1 ሺ 391.5 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍኑ ልዩ ልዩ የግንባታና የጥገና ስራዎችን በማከናወን የዕቅዱን 117 በመቶ አፈፃፀም አስመዝግቧል፡፡
የ2017 በጀት ዓመት ጥቅል የመንገድ ግንባታና ጥገና አፈፃፀም ከ2016 ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀርም የ25 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከ 370 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት የሚሸፍኑ ልዩ ልዩ የመንገድ ግንባታ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የተገነቡትን መንገዶች ጨምሮ 69.3 ኪሎ ሜትር የአስፋልት፣ 16 ኪሎ ሜትር የጠጠር እና 95.2 ኪሎ ሜትር የኮብል ንጣፍ መንገድ ስራ ተከናውኗል፡፡
በሌላም በኩል 107 ኪሎ ሜትር የነባር እግረኛ መንገዶች መልሶ ግንባታ ከመከናወኑም በተጨማሪ ከ79 ኪሎ ሜትር በላይ የፔዳል ሳይክል መንገድ የግንባታ ስራ ተካሄዷል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከግንባታ ስራዎች ጎን ለጎን፤ 110 ኪሎ ሜትር የአስፋልት፣ 23 ከ.ሜ የጠጠር፣ 29 ኪሎ ሜትር የኮብል መንገድ ጥገና አካሂደዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የጎርፍ አደጋ ስጋትን ለመከላከል 483 ኪሎ ሜትር የድሬኔጅ መስመር ፅዳትና ጥገና፣ እንዲሁም ከ19 ኪሎ ሜትር በላይ የእግረኛ መንገድ ጥገናና የከርቭ ስቶን ስራዎች በድምሩ 1021 ኪሎ ሜትር ልዩ ልዩ የጥገና ስራዎችን በበጀት ዓመቱ አጠናቆ ለትራፊክ ክፍት አድርጓል፡፡
