የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ሠራተኞች በ”አንድ ጀንበር 700 ሚሊዮን” ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በመሣተፍ አሻራቸውን አኑረዋል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አመራር እና ሰራተኞች “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል በዘንድሮው የአንድ ጀንበር 700 ሚሊዩን ችግኝ የመትከል መርሃ- ግብር ላይ ተካፋይ ሆነዋል።
በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 6 በቀድሞው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የግንባታ ግብዓት ማምረቻ ስፍራ ተሾመ ካባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የባለሥልጣኑ አመራርና ሠራተኞች አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩን ያስጀመሩት የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሙህዲን ረሻድ፤ የችግኞቹ መተከል የአየር ብክለትን ለመቀነስ፣ በክረምት ወቅት የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋና የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው ብለዋል፡፡
ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአጠቃላይ 20 ሺህ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዛሬው ዕለትም 11 ሺህ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በክረምት የተተከሉ ችግኞች በበጋው ወቅት ውሃ በማጠጣትና በመንከባከብ የጽድቀት መጠናቸውን ማሳደግና ለፍሬ ማብቃት ከሁሉም የተቋሙ ሠራተኞች እንደሚጠበቅ ዋና ዳይሬክተሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።
በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ ላይ የተሳተፉ የባለሥልጣኑ አመራርና ሠራተኞች ችግኝ መትከል ብዝሃ ህይወትን በማስቀጠል ረገድ አስተዋፅኦው ከፍ ያለ በመሆኑ ፤ የከተማዋን አረንጓዴ ሽፋን ለማሳደግ ለሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
