የቦሌ ሆምስ – ጎሮ የመንገድ ፕሮጀክት ገፅታዎች
ከቦሌ ሆምስ የቀለበት መንገድ ወደ ጎሮ አይ.ሲ.ቲ ፓርክ አቅጣጫ እየተገነባ የሚገኘው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በከተማዋ ከሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 4.9 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 60 ሜትር ጎን ስፋት ያለው ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ በሁለቱም አቅጣጫ 8 ተሸከርካሪዎችን ማስተናገድ ይችላል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱ የሰብ ቤዝ ግንባታ በአስፋልት ማካዳም ወይም ዲ.ቢ.ኤም የተሰራ እና የተደራቢ አስፋልት ማንጠፍ ሥራው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በአጠቃላይ 28 ሴንቲ ሜትር ውፍረት የሚኖረው በመሆኑ ጥራትና ጥንካሬው ከፍተኛ ይሆናል፡፡
በገደላማ የመንገድ ፕሮጀክቱ አካባቢዎች እስከ 12 ሜትር ከፍታ ያለው ረጅም የድጋፍ ግንብ በመገንባት ዳገትና ቁልቁለት እንዲቀንስ ተደርጎ የተሠራ በመሆኑ፤ ደህንነቱ የተጠበቀ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር አስችሏል፡፡
በተጨማሪም የፔዳል ሳይክል መተላለፊያ መስመሮች፣ ሰፊና ምቹ የእግረኛ መንገድ እና 12 ሜትር ስፋት ያለው የመንገድ አካፋይ አረንጓዴ ሥፍራን አካቶ እየተገነባ ሲሆን፣ አሁን ላይ የመጀመሪያ ደረጃ የአስፋልት ስራው ተጠናቆ በሁለቱም አቅጣጫ ለትራፊክ ክፍት ተደርጓል፡፡
አሁን ላይ የመንገድ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ የፊዚካል አፈፃፀሙም 90 በመቶ ደርሷል፡፡
በቀጣይ አጭር ጊዜም ቀሪዎቹን የእግረኛ እና የሳይክል መንገዶች ግንባታ እንዲሁም የመጨረሻውን የአስፋልት ንጣፍ ስራ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
