በካዛንቺስ ኮሪደር ላይ የህግ ጥሰት የፈፀመ የመኪና ኪራይ ድርጅት አንድ መቶ ሺህ ብር ተቀጣ
AMN – ግንቦት 4/2017 ዓ.ም
በካዛንቺስ ኮሪደር ላይ የህግ ጥሰት የፈፀመ የመኪና ኪራይ ድርጅት አንድ መቶ ሺህ ብር መቀጣቱን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዳኜ ሂርጳሳ እንደተናገሩት፣ አሽከርካሪዉ የህግ ጥሰቱን የፈጸመው ግንቦት 02 ቀን 2017 ዓ.ም ምሽት ሁለት ሰዓት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ካሳንቺስ አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሽከርካሪው የህግ ጥሰቱን ከፈጸመ በኋላ ቢያመልጥም የመኪና ኪራይ ድርጅቱ በህዝብ ጥቆማ ተደርሶበት ግንቦት 04 ቀን 2017 ዓ.ም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ተገኝቶ አንድ መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት መክፈሉንና ይቅርታ መጠየቁን ተናግረዋል፡፡
እንደ ክፍለ ከተማው የደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳኜ ሂርጳሳ ገለጻ፣ አሽከርካሪዉ ለጊዜዉ በህግ ቁጥጥር ስር ባይውልም ክትትል እየተደረገበት ነዉ፡፡
በክፍለ ከተማው ባለፉት ዘጠኝ ወራት አግባብነት በሌለው ሁኔታ በኮሪደር ልማት ላይ ጉዳት ባደረሱ አካለት እና አሽከርካሪዎች ላይ የ20 ሚሊየን ብር የገንዘብ ቅጣት እርምጃ መወሰዱን አብራርተዋል፡፡
አሽከርካሪዎችን ጨምሮ መላዉ የከተማው ህዝብ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የኮሪደር ልማት መሰረተ ልማቶችን ሊንከባከብ ይገባል ያሉት ኃላፊዉ በግዴለሽነት ጥፋት ፈጽመው ከህግ ለማምለጥ የሚሞክሩ አካላትን ነዋሪዉ ተከታትሎ ሊያጋልጥ እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ምንጭ፦ AMN
