+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የኮሪደር ልማት የአዲስ አበባን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭነት አሳድጓል

የኮሪደር ልማት ሥራው የአዲስ አበባ ከተማን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭነት ማሳደጉ ተገለጸ።

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው የናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና የግብጽ ዜግነት ያላቸው የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተሳታፊዎች እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ መሰረተ ልማት የተሟላ መሆን ለጎብኚዎች ምቾትን ይሰጣል።

ናይጄሪያዊው አዮ ዴኔሂ፤ በመዲናዋ የታዩ ፈጣን ለውጦች ከተማዋን በላቀ ደረጃ ለኮንፍረንስ ቱሪዝም ምቹ ማድረጉን ተናግሯል።

ከኮሪደር ልማት ባሻገር የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ የሁነት ማዘጋጃ ማዕከላት አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ የዘርፉን አካላት ለመሳብ መደላደል ስለመፍጠሩ ተናግሯል፡፡

ደቡብ አፍሪካዊቷ ኮንፊደንስ ሉኩዋኔ በበኩሏ፤ የዳበረ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ብዙ የሚጎበኝ ሀብት እንዳላት መመልከቷን ገልጻለች።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን ጨምሮ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በመጎብኘት የከተማዋን እምቅ የቱሪዝም አቅም መረዳቷንም ጠቁማለች።

አዲስ አበባ ከተማን ሶስት ግዜ ያህል የጎበኛት ሌላኛው ደቡብ አፍሪካዊ ሻተን ቲቻዎ በበኩሉ፤ ከተማዋ በማያቋርጥ ልማት ላይ መሆኗን መገንዘቡን ተናግሯል።

በተለይም ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ መንግስት እያከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማዋን ለኑሮ ምቹ ለጎብኚዎች ማራኪ እንድትሆን ማስቻሉን ገልጿል።

ይህም በከተማዋ ያለውን የጎብኚዎች ቁጥር ከማሳደግ አንጻርም የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ አስረድቷል።

ግብጻዊው አህመድ መሐመድ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ የሚታዩ አዳዲስ መንገዶችና ህንጻዎች መንግስት ለልማት ትኩረት የሰጠ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል፡፡

ኮንፈረንሶችን ጨምሮ በተለያየ ምክንያት ወደ ከተማዋ የሚመጡ ሰዎችን ቆይታ የሚያሳምር ሥራ መሰራቱን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማት ሥራዎቹ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በማስተናገድ ጥሩ ተሞክሮ ላላት ኢትዮጵያ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመዋል።

ምንጭ፦ FBC

Comments are closed.