+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ባለፉት 6 ወራት በተካሄዱ ተግባራት አፈፃፀም የባለድርሻ አካላትን ተሣትፎ መሠረት ያደረገ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አብረውት ከሚሰሩ ኮንትራክተሮች፣ ማህበራት፣ አቅራቢዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተቋሙ የአሰራር ግልፀኝነትና በሚያጋጥሙ ችግሮች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡

የውይይት መድረኩን የመሩት የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የተቋም ለውጥና ድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል ዶሌቦ፤ ባለስልጣኑ በበጀት ዓመቱ እያከናወናቸው የሚገኙ ልዩ ልዩ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ አገልግሎት አሠጣጡን ግልፅና አሳታፊ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ጋር ተያይዞ ማህበራት ለሚሰሯቸው ስራዎች ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ እውቅና እንደሚሰጥ የገለፁት አቶ ጀማል፤ ባለድርሻ አካላት ለብልሹ አሠራር የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን በጋራ በመታገል የተጣለባቸውን ኃላፊነት በጥራትና በብቃት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

በባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የሬጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ፀጋዬ ቦርሴ በበኩላቸው ማህበራት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በጥራትና በጊዜ ሲያጠናቀቁ፣ ራሳቸውን ለቀጣይ የስራ ዕድል ፈጠራ እያዘጋጁ መሆኑን ጭምር ሊረዱ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ባልተገባ ምክንያት ሥራ በሚያጓትቱ አካላት ላይ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በተቋሙ በኩል ለተፈጠረላቸው ዘርፈ ብዙ የስራ ዕድል ምስጋናቸውን አቅርበው፣ የክፍያ መዘግየትን ጨምሮ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ የአሰራር ክፍተቶች ታይተው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

Comments are closed.