+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የአንበሳ ጋራጅ – ጎሮ አደባባይ የኮሪደር ልማትን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም፡- ከአንበሳ ጋራጅ – በጃክሮስ – ጎሮ አደባባይ ድረስ እየተከናወነ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ቀሪ የግንባታ ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት በትጋት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር እና የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ኢንጅነር ሙህዲን ረሻድ ገልፀዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ዛሬ ማለዳ በቦታው ተገኝተው የኮሪደር ልማቱን የግንባታ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን፤ ባለፉት 3 ወራት በተካሄደው የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ የፔዳል ሳይክል መተላለፊያ መስመር፣ ሰፊና ምቹ የእግረኛ መንገዶች፣ የታክሲ ማውረጃና መጫኛ ተርሚናሎች፣ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች፣ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች፣ የአረንጓዴ ልማት እና በርካታ ተያያዥ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አብራርተዋል፡፡

አሁን ላይ የኮሪደር ልማቱ የግንባታ ሂደት 85 በመቶ ላይ መድረሱን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ቀሪ ስራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከቀኑ ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ በሌሊትም በከፍተኛ ርብርብ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከአንበሣ ጋራጅ ወደ ጎሮ የሚወስደው መንገድ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት የሚያስተናግድ የውጨኛው ቀለበት መንገድ መዳረሻ መሆኑን የጠቆሙት ኢንጂነር ሙህዲን፤ የኮሪደር ልማት ስራው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ለትራፊክ መጨናነቅ መንስኤ ሆነው የቆዩት የፓርኪንግ፣ የታክሲ መጫኛና ማውረጃ ቦታዎች፤ እንዲሁም የእግረኛ መንገዶች በዘመናዊ መልኩ ተሻሽለው እየተገነቡ በመሆናቸው ችግሩ በዘላቂነት ሊፈታ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

በሥፍራው እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት፤ ከቦሌ – መገናኛ እና ከሰሚት – ጎሮ ከሚሰራው ሌላኛው የኮሪደር ልማት ጋር የሚያስተሳስር በመሆኑ የሰሜናዊ ምሥራቁን የከተማዋን ክፍል ገፅታ በመቀየር እና የአካባቢውን አጠቃላይ የትራፊክ እንቅስቃሴ በማሳለጥ በኩል ሚናው የጎላ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ለኮሪደር ልማቱ ስኬት ህብረተሰቡ እስካሁን ላሳየው ቀና ትብብር እና የእኔነት ስሜት ዋና ዳይሬክተሩ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ በቀጣይም የፕሮጀክቱ ግንባታ ሙሉ በሙሉ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ቀና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

ዩቱዩብ: https://www.youtube.com/@addisababacityroadsauthori1369

ቲክቶክ፡- https://www.tiktok.com/@addisababaroads

ድረ-ገፃችንን ይጎብኙ ፡- https://www.aacra.gov.et

ለማንኛውም ጥቆማ ፡- 8267 ነጻ የስልክ መስመር ይጠቀሙ

Comments are closed.