በከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን መሠረት የመንገድ መሠረተ-ልማት ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ10ኛው የአዲስ አበባ መዋቅራዊ ፕላን መሠረት የከተማዋን 30 በመቶ ክፍል በመንገድ መሠረተ-ልማት ማስተሳሠርን ታላሚ በማድረግ እየተሠራ መሆኑን የአሥተዳደሩ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
በዚሁ መሠረት የከተማዋን የመንገድ ሽፋን ለማሳደግ ባለፉት ሥድስት ዓመታት የነባር መንገዶች ማሻሻያ እና የአዳዲስ መንገዶች ግንባታ መከናወኑን የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢያሱ ሰሎሞን ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም የቃሊቲ – ቱሉ ዲምቱ፣ የቂሊንጦ – ቃሊቲ፣ የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ – አይ.ሲ.ቲ ፓርክ፣ የአይ.ሲ.ቲ ፓርክ – አራብሳ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በባለሥልጣኑ አቅም የተገነቡ አጫጭር እና አንደኛውን ጎዳና ከሌላኛው የሚያስተሳሥሩ አዳዲስ መንገዶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አሁን ላይ እየተተገበረ ባለው የከተማዋ 10ኛው መዋቅራዊ ፕላን መሠረት 40 በመቶ የከተማዋ ክፍል ለግንባታ፤ 30 በመቶው ለመንገድ ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ ለአረንጓዴ ልማት ማዋልን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በዚሁ መሠረት ከከተማዋ አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን አንጻር እየተሠራ ያለው ሥራ ዋነኛ መነሻው የከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን መሆኑን ለፋና ዲጂታል አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል የኮሪደር ልማቱ ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች እንዲኖሩ ማስቻሉ፣ የፔዳል ሳይክል መተላለፊያ መሥመሮችን ማመቻቸቱ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረጉ ለከተማዋ ዕድገት አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ ተቋማት ተሣትፎ የመንገድ አካፋይና ዳርቻዎች በአረንጓዴ እፅዋት እንዲዋቡና ደማቅ ብርሃን ባላቸው የመንገድ ዳር መብራቶች መሸፈናቸው የከተማዋ ጎዳናዎች ዘመናዊና ማራኪ ገፅታ እንዲላበሱ ማስቻሉን አቶ ኢያሱ ጠቁመዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
