የቦሌ ኤርፖርት – ጎሮ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አፈፃፀም 90 በመቶ ደርሷል
የአዲስ አበባ ፣ የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ከቦሌ ብራስ የቀለበት መንገድ መጋጠሚያ ወደ ጎሮ አይ.ሲ.ቲ ፓርክ እየገነባው የሚገኘው የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡
የፕሮጀክቱ ግንባታ አሁን ላይ ከቦሌ ጉምሩክ ጀምሮ እስከ ጎሮ ባለው የመንገድ ፕሮጀክቱ ክፍል ላይ የሰብ ቤዝ፣ የከርቭ ስቶን፣ የድልድይ፣ የከልቨርት ቦክስና የድጋፍ ግንብ ስራዎች ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ የመጀመሪያ ደረጃ የአስፋልት ንጣፍ ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 4.9 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 60 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን፣ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ የውል ዋጋ በአሰር ኮንስትራክሽን እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን፣ የማማከርና የቁጥጥሩን ስራውን ደግሞ ዩኒኮን አማካሪ ድርጅት እየተከታተለው ይገኛል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱን ቀሪ የግንባታ ስራዎችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራም ይገኛል፡፡
