+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም የሰራተኞች ውይይት ተካሄደ

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንም በጋራ ተከብሯል;;

አዲስ አበባ፣ የካቲት15 ቀን 2017 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ሠራተኞች በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

የውይይት መድረኩን የመሩት የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሙህዲን ረሻድ፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የተከናወኑ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች የተሻለ አፈፃፀም እንደነበራቸው ገልፀዋል።

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በቀጣይም የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት መወጣት ይችል ዘንድ በቴክኖሎጂ፣ በአሰራርና በአደረጃጀት የተሻለ ተቋም ለመፍጠር፤ ተቋማዊ ሪፎርም ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ የጥናት ስራዎች ተጠናቀው ወደ ተግባር ለመግባት የቦርድ ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በስራ ተቋራጮች ሲገነቡ የነበሩና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ግንባታቸው የተጓቶ የቆዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች የገጠማቸውን ችግሮች በመፍታት የግንባታ ስራዎችን ማስቀጠል መቻሉን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይ ወራትም የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን ማጠናቀቅና በዕቅድ የተያዙ የግንባታና የጥገና ስራዎችን ከዳር ለማድረስ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት የተገኙ ስኬቶችንና መልካም ተሞክሮዎችን በማሳደግ በቀጣይ ወራትም የተቋሙን ውጤታማነት ለማስቀጠል ሁሉም የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች በላቀ ቅንጅትና በትጋት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው፤ የኑሮ ውድነት ጫናው የሠራተኛውን ህይወት በከፍተኛ ሁኔታ እየፈተነ መሆኑን ጠቁመው፤ የደመወዝ ማሻሻያ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

ባለፉት 6 ወራት የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል፣ ቀሪ ስራዎችን በቀጣይ ወራት ለማጠናቀቅ በላቀ የሥራ ተነሳሽነት ለመፈፀም ዝግጁ መሆናቸውን የውይይቱ ተሣታፊዎች አረጋግጠዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና መፈታት ይገባቸዋል ለተባሉ ሀሳቦች የየዘርፉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ምላሻ ሰጥተዋል፡፡

በዕለቱ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ‹‹ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል›› በሚል መሪ ቃል በጋራ የተከበረ ሲሆን፣ በ2017 በጀት ዓመት በጡረታ ለሚገለሉ ሴት ሰራተኞች የምስጋና የምስክር ወረቀት እና የማስታዎሻ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡

Comments are closed.