የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ባስተላለፋቸው ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ የሠራተኞች ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6 ቀን 2017፡- 2ኛው የብልፅግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎችና ባስተላለፋቸው ውሣኔዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የሠራተኞች የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች ተካሂዷል፡፡
የባለሥልጣን መስሪያቤቱ የተቋም ለውጥና ድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል ዶሌቦ በውይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለፁት፤ የብልጽግና ፓርቲ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ በሚሰራባቸው አበይት ተግባራት ላይ የመንግሥት ሠራተኛው በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጥና ለተግባራዊነታቸው በትጋት እንዲንቀሳቀስ ለማስቻል የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ያስተላለፋቸው ውሣኔዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሃገሪቱን ወቅታዊና አንገብጋቢ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚያስችሉ እንደሆኑ የጠቆሙት አቶ ጀማል፤ የባለሥልጣን መስሪያቤቱ አመራርና ሠራተኞችም ከተቋሙ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ተግባራዊ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የአመራርና የሠራተኛውን ጥራትና ብቃት በማሳደግ፣ በብሔራዊነት ገዥ ትርክት፣ በሠላም ግንባታ፣ በፍትህ ዘርፍ ውጤታማነት፣ የሀገር ግንባታን በማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ልማትን በማፋጠን፣ ማህበራዊ ብልፅግናን በሚያረጋግጡ ሥራዎች፣ በውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራዎች፣ በሲቪል ሰርቪስ ውጤታማነት እና በጠንካራ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በአስር የተለያዩ መድረኮች ላይ በተካሄደው በዚህ ውይይት ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ የተቋሙ ሠራተኞች የተካፈሉ ሲሆን፤ በፓርቲው አመራር ባለፉት ዓመታት በተለያዩ መስኮች አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ የውይይቱ ተሣታፊዎች ጠቁመው፤ በሁለተኛው የብልፅግና ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን ወደ ተግባር ለመቀየር የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
