+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

በደቡብ አዲስ አበባ በመንገድ ዘርፍ የተሰማሩ ማህበራትና አማካሪ ድርጅቱ ላሳዩት መልካም አፈፃፀም እውቅና ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም፡- በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች በተከናወኑ የመዳረሻ መንገድ እና የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ግንባታ ስራዎች ላይ የተሳተፉ መልካም አፈፃፀም ላስመዘገቡ የመንገድ ዘርፍ ሥራ ማህበራትና ለአማካሪ ድርጅቱ የእውቅና እና የምስጋና መርሃ-ግብር ተካሄደ፡፡

የእውቅና እና የምስጋና መርሃ-ግብሩ የተካሄደው በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በደቡብ አዲስ አበባ መንገድ ሀብት አስተዳደር ነው፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመንገድ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር

ኢንጂነር መሀመድ አወል፤ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በከተማዋ በስፋት እያከናወናቸው ከሚገኙ የአስፋልት መንገድ ግንባታ እና ጥገና ስራዎች በተጨማሪ፣ የመንገድ መሠረተ-ልማት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ለህብረተሰቡ የመውጫና መግቢያ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ፤ የጠጠር መንገዶችን ከመገንባት ጎን ለጎን የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል የድሬኔጅ መስመር ግንባታ እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች የተከናወኑት የአክሰስ መንገድ እና የድሬኔጅ መስመሮች ግንባታ ይህን ተግባር ከሚያመላክቱ ማሳያዎች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በሥራው ላይ የተሳተፉ ማህበራት እና ጎንድዋና አማካሪ ኢንጅነሪግ፣ በግንባታ ሥራው ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በመቋቋም ላስመዘገቡት የተሻለ አፈፃፀም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የደቡብ አዲስ አበባ መንገድ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር ኢንጅነር ህይወት ሳሙኤል በበኩላቸው፤ በ2016 በጀት ዓመት በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች 30 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የአክሰስ መንገድ እና 2 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የድሬኔጅ መስመር ግንባታ ስራ ማከናወን መቻሉን ገልፀው፤ በዚህም 70 ሺ የሚሆኑ ነዋሪዎችን በመንገድ መሰረተ ልማት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል ።

በሁለቱም ክፍለ ከተሞች በተከናወኑ የመቃረቢያ መንገድና የድሬኔጅ መስመሮች ግንባታ ሥራ ላይ 29 ማህበራትና አንድ አማካሪ ድርጅት መሳተፋቸውን የገለፁት ኢንጅነር ህይወት፤ በሥራው የተካፈሉ አካላት በትጋት በመስራት ላስመዘገቡት ውጤት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ እውቅና የተሰጣቸው ማህበራትና አማካሪ ድርጅቶች በበኩላቸው፤ የተሰጣቸው እውቅና ለወደፊቱ በተሻለ የሥራ ተነሳሺነት የላቀ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ጠንክረው እንዲሰሩ የሚያተጋ መሆኑን ገልፀው፤ ለዝግጅቱ አስተባባሪዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

ዩቱዩብ: https://www.youtube.com/@addisababacityroadsauthori1369

ቲክቶክ፡- https://www.tiktok.com/@addisababaroads

ድረ-ገፃችንን ይጎብኙ ፡- https://www.aacra.gov.et

ለማንኛውም ጥቆማ ፡- 8267 ነጻ የስልክ መስመር ይጠቀሙ

Comments are closed.