19ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በፓናል ውይይት ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም፣- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አመራርና ሠራተኞች ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሄር-ብሄረሰቦችን ቀን በፓናል ውይትና ሌሎች ዝግጅቶች በድምቀት አክብረዋል።
“አገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በተዘጋጀው የብሔር፣ ብሔረሰቦች ቀን በዓል ላይ “ህብረ-ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት በኢትዮጵያ፤ ተግዳሮቶቹና የመፍትሄ ሃሳቦች” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የተቋም ለውጥና ድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል ዶሌቦ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ በሀገራችን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን መከበሩ፣ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ባህልና ወጋቸውን እርስ በእርስ ለመተዋወቅ መልካም አገጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አቶ ጀማል አያይዘውም፤ በሀገራችን የጀመርነው የእድገትና ብልፅግና ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በተለያዩ አካባቢዎች ለሠላም እጦት ምክንያት የሆኑ ልዩነቶች ከግጭት ይልቅ በውይይት በሚፈቱባቸው ሁኔታዎች ላይ ማተኮርና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዕለቱን አስመልክቶ የውይይት መነሻ ሰነድ ያቀረቡት የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ሰሎሞን፤ የሀገሪቱን የፌዴራል አስተዳደር ሥርዓት ለማፅናት እና በኢትዮጵያ ህዝቦች ይሁንታ በማሻሻል ዘላቂ ሀገረ-መንግሥት ለመገንባት፣ ብዝሃነትን ማክበርና እኩልነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ባለፋት 30 ዓመታት በሀገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት አተገባበር የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስቀጠልና ለህብረ-ብሔራዊ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶችን በመፍታት በኩል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በጋራ ሊሰራ እንደሚገባም አቶ ኢያሱ ጠቁመዋል፡፡
የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ሠራተኞች በቀረበው ሰነድ ላይ ትኩረት በማድረግ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፤ ለፌዴራል ሥርዓቱ መጠናከር እና የሚገጥሙ ፈተናዎችን ለመሻገር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የዜግነት ድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡