የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት የሚያግዝ የመስክ ጉብኝት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከፍተኛ አመራሮች ከሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ያጋጠማቸውን የወሰን ማስከበር እና ተያያዥ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል የመስክ ጉብኝት አካሂደዋል፡፡
በባለሥልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር የተመራው የባለድርሻ አካለት ቡድን በትላንትናው ዕለት የሲ.ኤም.ሲ – ወጂ መድሐኒዓለም፣ የአይ.ሲ.ቲ ፓርክ – ቦሌ አራብሳ፣ የቦሌ ኤርፖርት ጎሮ እና የእንግሊዝ ኤምባሲ – 22 ቦሌ ኤድናሞል የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሙህዲን ረሻድ በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ያጋጠሙ የወሰን ማስከበር እና ሌሎች ችግሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፈተው የግንባታ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችል የሥራ መመሪያ መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም የአውቶብስ ተራ -መሳለሚያ – 18 ማዞሪያ እና የአየር ጤና – ወለቴ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በባለሥልጣኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ በስራ ተቋራጮች፣ በአማካሪ መሀንዲሶች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክፍለ ከተማ አመራሮች የተጎበኙ ሲሆን፣ ያጋጠሙ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡