ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን አስመልክቶ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አመራርና ሠራተኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ እየተከበረ በሚገኘውን የዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን ” ወጣቶችን ያማከለ የፀረ ሙስና ትግል ፤ የነገን ስብዕና ይገነባል” በሚል መሪ ሃሳብ በውይይት አክብረዋል፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሙህዲን ረሻድ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ ሙስና ስልጣንና ኃላፊነትን ያለአግባብ በመጠቀም፣ ውስን የሆነውን የሀገር ሀብት ለራስና ለሌሎች ጥቅም ተጋሪዎች በማዋል በሀገርና በህዝብ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የማድረስ አፍራሽ ተግባር በመሆኑ፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በንቃት ሊታገለው እንደሜገባ አሳስበዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለሙስና እና ብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ ሁኔታዎችን በመለየት የማስተካከያ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ጠቁመው፣ በላቀ አደረጃጀትና በቴክኖሎጂ የታገዘ የተሻለ የአሰራር ስርዓት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን በመጥቀስ፤ ሁሉም የተቋሙ ሰራተኞች ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን በመጠየፍ የህብረተሰቡን እርካታ የሚያረጋግጥ አገልግሎት ለመስጠት እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዕለቱን አስመልክቶ የውይይት የመነሻ ሰነድ ያቀረቡት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ባለሞያ አቶ ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው፤ ሙስና ህግና ስርዓትን ተከትሎ ከመስራት ይልቅ፣ ሥልጣንና ኃላፊነትን መከታ በማድረግ የሚፈፀም ድንበር የለሽ ዓለም አቀፋዊ ወንጀል በመሆኑ፤ እንደ ሀገር ሙስናን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅበት ገልፀዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራርና ሰራተኞች በበኩላቸው በተሰማሩበት የስራ መስክ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡