የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህፃናት ማቆያ ማዕከል ተመረቆ ተከፈተ
ሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በዋናው መስሪያ ቤት ከ500 ሺ ብር በላይ በሆነ ወጪ ያቋቋመው የህፃናት ማቆያ ማዕከል በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ፡፡
በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በባለስልጣኑ የተቋም ለውጥና ድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል ዶሌቦ በተቋሙ የህፃናት ማቆያ መጀመሩ የሴት ሰራተኞችን ጥያቄ የመለሰና ያለባቸውን ጫና በማቃለል በተሰማሩበት የስራ መስክ ምርታማ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋፆኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል፡፡
አቶ ጀማል አያይዘውም የህፃናት ማቆያው ስራ መጀመሩ ለሴት ሰራተኞች የስራ እድል የፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤በቀጣይ በሌሎች የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ ቦታዎች ላይ ለማቋቋም እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
በባለስልጣኑ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ቡድን መሪ የሆኑት ወይዘሪት ፀደንያ አበበ በበኩላቸው ሴት ሰራተኞች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ስራ እስከመልቀቅ እንደሚደርሱ አስታውሰው፤ አሁን ላይ ማቆያው በመቋቋሙ ይገጥማቸው የነበረውን ችግር ከማቃለሉ ባለፈ ህፃናቱ በቅርበት የእናታቸውን እንክብካቤ አግኝተው፣ ደህንነታቸውና ጤንነታቸው ተጠብቆ እንዲያድጉ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ የመጡት ወይዘሮ ብርሀን ሎዮ እንደገለፁት በመዲናዋ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ጨምሮ 176 የህፃናት ማቆያ በተለያዩ ተቋማት መከፈቱን ገልፀው፤ በመስሪያ ቤቶች የህፃናት ማቆያዎች መከፈታቸው ህፃናት ጤንነታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲያድጉ ትልቅ አስተዋፆኦ የሚያበረክት በመሆኑ እንደሀገር ብቁ ዜጋ ለማፍራት መንደርደሪያ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች በበኩላቸው የሕፃናት ማቆያው በመከፈቱ ለሴት ሰራተኞቹ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/
ዩቱዩብ:- https://www.youtube.com/@addisababacityroadsauthori1369