ባለስልጣኑ ከ1.9 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን የመንገድ ፕሮጀክቶች በይፋ አስመረቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27 ቀን 2014 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በራስ ኃይልና በስራ ተቋራጮች ከ1.9 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸው በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በይፋ አስመርቋል፡፡በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል 9 መንገዶች፣ 2 የመኪና ማቆሚያዎች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የመንገድ ዳር መብራቶች እና የእንጦጦ አምባ ት/ቤት የአስተዳደር ህንፃ ይገኙበታል፡፡ እነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች የእግረኛ መንገዶችንና የመኪና ማቆሚያዎችን ሳይጨምር 19.12 ኪ.ሜ ርዝመት እና ከ13 እስከ 60 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት አላቸው፡፡ከፕሮጀክቶቹ መካከል የመኪና ማቆሚያዎችን ጨምሮ 8 የሚሆኑት በባለስልጣኑ የራስ ሀይል የተገነቡ ሲሆን ቀሪዎቹ በተለያዩ የስራ ተቋራጮች ተገንብተው የተጠናቀቁ ናቸው፡፡