በፒያሳና አካባቢው ሲካሄድ የቆየው የመንገድ ማሻሻያ ግንባታ ተጠናቀቀ
የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በፒያሳና አካባቢው ሲያካሂድ የነበረውን የመንገድ ማሻሻያ ግንባታ ሥራ አጠናቆ መንገዱን ለትራፊክ ክፍት አድርጓል፡፡
ከአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ ወደ ቸርችል ጎዳና የሚያገናኘውን የነባር መንገድ አቅጣጫ በመለወጥ 315 ሜትር ርዝመት ያለው አጭርና አቋራጭ መንገድ ተገንብቶ ለአገልግሎት በቅቷል፡፡
ቀደም ሲል አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውና ወደ አሮጌው ፖስታ ቤት የሚወስደው ነባር መንገድ ጠመዝማዛ እና ተዳፋት በመሆኑ ለትራፊክ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በአካባቢው የነበረውን የትራፊክ ፍሰት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ ወደ ቸርችል ጎዳና በቀጥታ የሚያገናኝ አጭርና አቋራጭ መንገድ ገንብቷል፡፡
ደህንነቱ የተጠበቀ ቀልጣፋ የትራፊክ ፍሰት ለመፍጠር ታስቦ ከተገነባው ከዚህ አዲስ አቋራጭ መንገድ በተጨማሪ በአድዋ ሙዚየም ዙሪያ እና አካባቢው 1.47 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን የአስፋልት መንገድ ማሻሻያ ጥገና ሥራ ተከናውኗል፡፡
በቀንና በሌሊት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው ይህ መንገድ፤ ቀደም ሲል በአካባቢው የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር የሚፈታ ከመሆኑም ባሻገር፣ ወደ አድዋ ሙዚየም የሚጓዙ ጎብኚዎች በተሻለ የትራፊክ ፍሰት ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ነው፡፡
በፒያሳና አካባቢው የተከናወነው የመንገድ ማሻሻያ ግንባታ፤ ከተሽከርካሪ መተላለፊያ መንገዶች በተጨማሪ 386 ሜትር ርዝመት እና እስከ 8 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት ያላቸው ሰፋፊና ውብ የእግረኛ መንገዶችን አካቶ የተገነባ በመሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ለትራፊክ አደጋ በማያጋልጥ መልኩ በእግር እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
በፒያሳና አካባቢው እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ ፍሰት በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማስተናገድ ቀደም ሲል የደጎል አደባባይን በማንሳት በትራፊክ መብራት የመቀየር እና ሌሎች ተያያዥ የመንገድ ማሻሻያ ሥራዎች በስፍራው መከናወናቸው ይታወሳል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity