በወንዞች ዳርቻ አፈር ማከማቸት በከተማዋ የጎርፍ አደጋ እንዲከሰት ምክንያት እየሆነ ይገኛል!
አዲስ አበባ፣ ህዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም፡- በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የወንዞች ዳርቻ አካባቢ ግለሰቦች ለሚያከናውኗቸው ልዩ ልዩ ግንባታዎች አስቆፍረው የሚያወጡትን አፈርና የግንባታ ተረፈ ምርት ያለገደብ በመድፋታቸው የተነሳ በከተማዋ የጎርፍ አደጋ እየተበራከተ ይገኛል፡፡
በወንዞች ዳርቻ አካባቢ ከልክ ያለፈ የአፈር ቁልል ወንዞች ተፈጥሯዊ ፍሰታቸውን ጠብቀው እንዳይሄዱ በማድረግ በክረምት ወቅት በወንዝ ዳርቻዎች አካባቢ ለሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የጎርፍ ስጋትን ከመፍጠሩም ባሻገር ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡
ለአብነትም ህዳር 8 ቀን 2016ዓ.ም በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ሰፈራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሰዓት በኋላ የጣላው ዝናብ ተከትሎ በተፈጠረ የጎርፍ አደጋ 18 የመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱ ለዚህ ሀላፊነት ለጎደለው ተግባር አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ችግሩን ለማቃለል በከፍተኛ ርብርርብ የአፈር ደለሉን የማፅዳት ስራ አከናውኗል፡፡
በመሆኑም ዛሬ ላይ ጥቂት ግለሰቦች ከሚያገኙት ጊዜያዊ ጥቅም ይልቅ ነገ ላይ እንደማህበረሰብ የሚፈጠረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከወዲሁ በማሰብ በሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች በሚገኙ ወንዞች ላይ አፈርና ሌሎች ተረፈ ምርቶችን ያለገደብ ማከማቸት በአስቸኳይ ሊቆም የሚገባ ተግባር ነው፡፡
በተመሳሳይም በሌሎች የወንዞች መፋሰሻ መስመሮችና በድልድዮች አካባቢ የሚከናወኑ ህገ-ወጥ ተግባራት የጎርፍ አደጋ ስጋት በመደቀን በሰው ህይወት፣ በንብረትና በመንገድ መሰረተ-ልማት ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና የከተማዋ ነዋሪዎች የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና እንዲወጡ ባለስልጣኑ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity