የዘመን መለወጫን በዓል አስመልክቶ የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም ተካሄደ
መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፤ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የ2016 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም አካሂዷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ የምገባ ማዕከላት መካከል አንዱ በሆነውና በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ውስጥ በሚገኘው የምገባ ማዕከል ቁጥር 5 በተካሄደው የማዕድ ሥነ-ስርዓት ላይ 500 የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡
በማዕድ ማጋራት ሥነስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሞገስ ጥበቡ እንደገለፁት፤ በከተማዋ የሚገኙ አቅመ ደካሞችን መደገፍ የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል የሞራል ግዴታ መሆኑን ጠቁመው፣ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣንም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለዘመን መለወጫ በዓል የምሳ ፕሮግራም ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ማህበራዊ ችግሮች በመንግሥት አቅም ብቻ የሚፈቱ ባለመሆኑ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ለበጎነት ተግባር እጃቸውን በመዘርጋት የአቅመ ደካሞችን የኑሮ ጫና በማቃለል በኩል የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሴቶችና ህፃናት ጽ/ቤት ኃላፊ እና የወረዳው ዋና ሥራ አስፈፃሚ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በአዲስ ዓመት የማዕድ ማጋራት ማካሄድ በመቻሉ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ይህ አርዓያነት ያለው ተግባር ወደፊትም በሌሎች አካላትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity