የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለጉዳዮች ባገኙት አገልግሎት መደሰታቸውን ገለፁ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 1 ቀን 2015 ዓ.ም፡- በአገልጋይነት ቀን ወደ አዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የመጡ ባለጉዳዮች ባገኙት የአገልግሎት አሰጣጥ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡
የባለሰልጣን መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች “ኢትዮጵያን እናገልግል” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ በሚገኘው የአገልጋይነት ቀን ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በዕለቱ እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት በስራ ገበታቸው ላይ ሆነው ባለጉዳዮችን ሲያስተናግዱ ያመሻሉ፡፡
አገልጋይነት የአንድ ቀን ተግባር ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት የስራ መስክ የሁልጊዜም መርሁ አድርጎ በቅንነት እና ከአድሎ በፀዳ መልኩ በተሰጠው ስልጣን እና ኃላፊነት ማገልገል እንዳለበትና መልካም አገልግሎት የመንፈስ እርካታ የሚያስገኝ ተግባር በመሆኑ ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ሊከተለው የሚገባ መርሆ መሆኑን ያነጋገርናቸው ባለጉዳዮች ገልፀውልናል፡፡
አቶ ኃይሉ ደበሌ ከመንገድ መሰረተ ልማት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ለማስፈፀም ወደ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መምጣታቸውን ገልፀው፣ ተገቢውን አገልግሎት ከመልካም መስተንግዶ ጋር ማግኘታቸውን ገልፀው ይህን መሰል አገልግሎት መቀጥል የሚገባው ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሌላው ተገልጋይ አቶ ገመቹ መሐመድ በበኩላቸው በቅንነት እና በጥሩ ስነ-ምግባር መስተናገዳቸውን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በዋናው መስሪያቤት እና በመንገድ ሃብት ቅርንጫፎች ተመሳሳይ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ በሌላም በኩል በልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎቹ አማካኝነት የአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎችን የማስዋብ፣ የመጠገን እና ለትራፊክ እንቅስቃሴ ምቹ የማድረግ ተግባራትን በስፋት እያከናወነ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/
