የከተማዋ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የመንገድ ግንባታና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ሐምሌ 2 ቀን 2015 ዓ.ም፡- በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ከፍተኛ ግብር ከፋዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመዲናዋ እየተገነቡ የሚገኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
ጉብኝቱን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ በከተማዋ 469 ሺ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ገልፀው፣ ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ በሚያመነጨው ሀብት በከተማዋ እየተገነቡ የሚገኙ መሰረተ-ልማቶችና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ተዘዋውረው እንዲጎበኙ ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን ገልጸው፣ ይህም በግብር ከፋዩ እና በግብር ሰብሳቢው መካከል የተሳለጠ ግንኙነት እንዲኖር ያግዛል ብለዋል፡፡
ጉብኝት ከተደረገባቸው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል የቃሊቲ አደባባይ ቡልቡላ ቂሊንጦ አደባባይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡
ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ሲጠናቀቅ የከተማዋን የወጪ ገቢ ኮሪዶር አማራጭ ከማስፋቱም በተጨማሪ ከኮዬ ፈጬ፣ ቱሉ ዲምቱ እና አካባቢው ወደ መሐል ከተማ ለሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች አቋራጭ መንገድ በመሆን እንደሚያገለግል የገለፁት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢያሱ ሰሎሞን ናቸው፡፡
አሁን ላይ በደቡብ አዲስ አበባ ክፍል 26.6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከ5.4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነቡ መሆናቸውን ለተሳታፊዎቹ የገለፁት አቶ ኢያሱ ለመንገዶቹ ግንባታ መሳካት የግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የሚያደርገው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የከተማዋ ግብር ከፋይ ማህበረሰብ ለከተማችን ሁለንተናዊ ዕድገት ሲባል በቅንነትና በታማኝነት ለሚያደርጉት አበርክቶም አቶ ኢያሱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity