አዲስ አበባ ከተማ የሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሳደግ እያከናወነችው ባለው የመንገድ መሰረተ-ልማት የብሉምበርግ ኢንሺዬቲቭ ሽልማት አሸናፊ ሆነች።
በዓለማችን የካርበን ልቀትን መቀነስና የትራንስፖርት አማራጮችን በማስፋት ለሰው ልጆች ጤንነት መጠበቅ አስተዋፀኦ ማድረግን ታሳቢ ባደረገው የብሉምበርግ ብስክሌት መሰረተ ልማት Bloomberg Initiative for Cycling Infrastructure (BIC) ኢንሼቲቭ አሸናፊ ከሆኑ 10 የዓለማችን ከተሞች ውስጥ አንዷ አዲስ አበባ ከተማ ሆናለች፡፡
በውድድሩ በአምስት አህጉራት የሚገኙ 275 ከተሞች የትግበራ አመላካች ዕቅድ በማቅረብ የተሳተፉ ሲሆን፣ በመመዘኛ መስፈርቱ መሰረት 10 ከተሞች የውድድሩ አሸናፊ ሆነዋል።
የብሉምበርግ ኢንሺዬቲቭ አሸናፊ ሃገራት፥ ኢትዮጵያን ጨምሮ ብራዚል፣ ህንድ፣ ጣሊያን፣ አልባኒያ፣ ኒውዝላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ኮሎምቢያ፣ ኬንያ እና ሞዛምቢክ ናቸው፡፡
አዲስ አበባ ከተማ በአፍሪካ ትልቁን የሳይክል ጎዳና ለመገንባት የጀመርቻቸው ስራዎችና ወደፊት ይህን ስኬት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ያቀረበችው ፕሮፖዛል አሸናፊ አድርጓታል።
የአየር ንብረት ለውጥ መከላከልንና ለህዝቡ ተጨማሪ የትራንስፖርት አመራጭ ማቅረብን ታሳቢ ባደረገው በዚህ ኢንሺዬቲቭ አዲስ አበባ ከተማ የ4ዐዐ ሺህ ዶላር ታገኛለች፡
አሸናፊዎቹ ከተሞች ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የቴክኒክ ድጋፍ የሚሰጣቸው ይሆናል::
ከተሞቹ ከብሉምበርግ ኢንሺዬቲቭ በሚያገኙት ድጋፍ የብስክሌት መጓጓዣ ጎዳናዎችን በመገንባት የነዋሪዎችን ጤና እና ደህንነት ለማጠናከር እንዲሁም ለዘላቂ ትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚያውሉት ይጠበቃል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የሞተር አልባ ትራንስፖርት እንቅስቃሴን ለማበረታታት ቀደም ሲል ከኃይሌ ጋርመንት ወደ ጀሞ 2 አደባባይ በሚወስደው ጎዳና ላይ 4.5 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን የመሄጃና መመለሻ የፔዳል ሳይክል መተላለፊያ መንገድ ገንብቶ ለአገልግሎት ያበቃ ሲሆን፣ አሁን ላይ ደግሞ ከቦሌ ኤርፖርት ወደ ጎሮ በሚወስደው አዲስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ውስጥ የፔዳል ሳይክል መተላለፊያ መስመርን አካቶ በመግባት ላይ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity