+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የቦሌ ሚካኤል ተሻጋሪ ድልድይ የቀኝ መስመር ለትራፊክ ክፍት ሆነ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም፡- በአዲስ አበባ ከተማ በውስጠኛው ቀለበት መንገድ ላይ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ለመፍታት እየተገነቡ ከሚገኙ የመንገድ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድዮች መካከል በርዝመቱ ቀዳሚ የሆነው የቦሌ ሚካኤል ተሻጋሪ ድልድይ የቀኝ መስመር ለትራፊክ ክፍት ሆኗል፡፡

ቀደም ሲል የማሳለጫ ድልድዩ የግራ መስመር ለትራፊክ ክፍት መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ላይ በቀኝ በኩል ያለው የማሳለጫ ድልድዩ ግንባታ በከፊል ተጠናቆ ለትራፊክ አገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡

ቡልቡላ ካባ መግቢያ -ቦሌ ሚካኤል የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አካል የሆነው የቦሌ ሚካኤል አደባባይ የላይና የታች መንገድ 600 ሜትር ርዝመት ያለው ተሸጋጋሪ የማሳለጫ ድልድይን ጨምሮ በአጠቃላይ 4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ ለፕሮጄክቱ ግንባታ ማስፈጸሚያ ከ720 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለታል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱን አሰር ኮንስትራክሽን እየገነባው የሚገኝ ሲሆን፣ የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ደግሞ ሀይ ዌይ ኢንጂነርስ አማካሪ ድርጅት እየተከታተለው ይገኛል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ ካለው አጠቃላይ ርዝመት ውስጥ 2 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የሚሆነው የመንገድ ክፍል የግንባታ ስራው ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን፣ ቀሪ የግንባታ ስራዎችንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማገባደድ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ከሳሪስ አቦ ወደ መገናኛ አቅጣጫ እና ከቦሌ ሩዋንዳ አቅጣጫ ወደ ቡልቡላ እንዲሁም ወደ ሌሎች የአካባቢው መዳረሻዎች በሚደረገው ጉዞ ላይ ይፈጠር የነበረውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ችግር በተሻለ ደረጃ እንደሚያቃልለው ይታመናል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.