ባለስልጣኑ ለአቅመ ደካማ ነዋሪዎች የገነባውን የጋራ መኖርያ ህንፃ አስመረቀ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2015ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከቂርቆስ ክ/ከተማ ጋር በመተባበር ሰላም ጎዳና አከባቢ ለአቅመ ደካማ ነዋሪዎች የገነባውን የአንድ ብሎክ ባለ ሶስት ወለል የጋራ መኖርያ ህንፃ በዛሬው ዕለት አስመረቀ፡፡
የምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤን ጨምሮ ሌሎች የከተማዋ ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት የጋራ መኖሪያ ህንፃው ተመርቆ ለአቅመ ደካማ ነዋሪዎች ተበርክቷል፡፡ በተጨማሪም ለመጪው የገና በዓል መዋያ የሚሆን በግ፣ ዶሮ፣ ዱቄት እና ዘይት ተበርክቶላቸዋል፡፡
የመኖሪያ ህንፃውን በቦታው ተገኝተው በይፋ ያስመረቁት ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ከወሎ ሰፈር አደባባይ እስከ ኡራኤል ቤተክርስቲያን ድረስ ውብ የሆነ መንገድ ተሰርቶ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ አቅመ ደካማ ሰዎች በተጎሳቆለ ኑሮ እንዲኖሩ መፍቀድ አብሮ የሚሄድ አይደለምና የሰዎችን ኑሮ መቀየር መቻል ትልቅ እርካታ የሚሰጥ በመሆኑ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራርና ሰራተኞች ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የቤት ቁልፍ የተበረከተላቸው ነዋሪዎች በበኩላቸው ቀደም ሲል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ፣ በክረምት ወቅት በጎርፍ እና በተለያዩ ምክንቶች ምቹ ባልሆነ መኖሪያ ቤት ለረጅም ዓመታት ይኖሩ እንደነበር አስታውስው ዘመናዊ የቤት ባለቤት በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡
ይህ የጋራ መኖርያ ቤት ፕሮጀክት በሀምሌ ወር 2014 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን አጠቃላይ በ 445 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈ ነዉ፡፡ህንፃው 21 የመኖሪያ ቤት እና 3 ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ ሱቆችን ያካተተ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity