በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ የሚገኙ መቃረቢያ መንገዶች የነዋሪዎችን የእለት ከእለት እንቅስቃሴ እያቀላጠፉ ነው
አዲስ አበባ – ጥር 30/2014 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የነዋሪዎችን የእለት ከእለት እንቅስቃሴ የሚያቀላጥፉና አንድን አካባቢ ከሌላው አካባቢ የሚያስተሳስሩ የጠጠር መንገድ ግንባታ ስራዎችን በስፋት እያከናወነ ይገኛል፡፡ እነዚህ በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ የሚገኙ የመቃረቢያ መንገዶች የህብረተሰቡን የመንገድ መሰረተ ልማት ይሟላልን ጥያቄ የሚመልሱ ናቸው፡፡ በተለይም ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለተጠቃሚው በሚፈለገው ጊዜና ፍጥነት ለማቅረብ የሚያግዙ ናቸው፡፡ የመቃረቢያ መንገዶቹ ቀድሞ ከነበሩበት የመንገድ ደረጃ ተሻሽለውና ሰፍተው በጠጠር መንገድ ደረጃ በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡ከኤካ ኮተቤ አማኑኤል ሆስፒታል እስከ ሚልኮን ካባ እንዲሁም ከሠላም ህፃናት መንደር እስከ ቁሊቲ ሚካኤል እየተገነባ የሚገኘው የጠጠር መንገድ ግንባታ የዚሁ ስራ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ መንገዱ በጠቅላላው 5 ኪሎ ሜትር ርዝመትና ከ8 እስከ 10 ሜትር የጎን ስፋት ኖሮት እየተገነባ ይገኛል፡፡በስፍራው አግኝተን ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለፁት ነባሩ መንገድ ጠባብ እና ለእንቃስቃሴ ምቹ ካለመሆኑ የተነሳ የትራንስፖርት አገልግሎትም ሆነ ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማግኘት በእግራቸው ረጅም መንገድ ይጓዙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ግንባታው በሁለት ሀገር በቀል የስራ ተቋራጮች አማካኝነት እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን ጎንዱዋና ኢንጂነሪንግ የተባለ ድርጅት የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ስራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡