የባለስልጣን መስርያቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች የደም ልገሳ መርሃ-ግብር አካሄዱ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 02 ቀን 2014 ዓ.ም፡- “ጳጉሜን በመደመር” በሚል መሪቃል የበጎ ፍቃድ ቀንን ምክንያት በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አመራሮችና ሠራተኞች የደምልገሳ መርሀ ግብር አካሂደዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ሰሎሞን በመርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ባለሥልጣን መስሪያቤቱ በ2014 ክረምት ወራት በችግኝ ተከላ፣ በአቅመ ደካሞች የቤት እድሳት፣ በደም ልገሳ፣ በህፃናት ድጋፍ እና በማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የውስጥ ለውስጥ መንገድ ጥገና የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የተቋሙን ሠራተኞች በማስተባበር እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ባለሥልጣን መስሪያቤቱ ጳጉሜ 3 ቀን በሚያካሄደው የምስጋና እና የእውቅና ኣስጣጥ ስነ-ስርዓት ላይ የተቋሙ ሠራተኞች በቋሚነት ለሚደግፋቸው 50 ህፃናት የአዲስ ዓመት ስጦታ የሚያበረክቱ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ በ2014 በጀት ዓመት ባስመዘገበው ከፍተኛ አፈፃፀም የላቀ አስተዋፅኦ ለነበራቸው ሠራተኞች እውቅና እንደሚሰጥ አቶ ኢያሱ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ባለስልጣን መስሪያቤቱ በ2014 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን የመንገድ ግንባታና ጥገና ዋና ዋና ተግባራት የሚያሳይ የፎቶ ግራፍ አውደ-ርዕይ በይፋ ተመርቆ ለዕይታ ክፍት ሆኗል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም: https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ : https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር : https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡ https://www.instagram.com/addisababaroads/
