የቦሌ ሚካኤል ተሸጋጋሪ ድልድይ
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በመዲናዋ ቀለበት መንገድ ላይ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናቅ ለመቀነስ የሚያስችል ስልት ቀይሶ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተለይም ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት እያያስተናገዱ በሚገኙ የመንገድ መጋጠሚያዎች ላይ ተሸጋጋሪ ድልድዮችን በመገንባት ፍሰቱ የተሳለጠ እንዲሆን የማድረግ ስራ እያከናወነ ነው፡፡ ለዚህም የቦሌ ሚካኤል ተሸጋጋሪ ድልድይ ግንባታ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በቦሌ ሚካኤል የመንገድ መጋጠሚያ ላይ እያንዳንዳቸው በ600 ሜትር ርዝመትና በ9 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖራቸው ዲዛይን ተደርጎ እየተገነቡ ከሚገኙ ተሸጋጋሪ ድልድዮች መካከል በአንድ አቅጣጫ ያለው ድልድይ ግንባታ በታህሳስ ወር 2014 ተጠናቅቆ ለትራፊክ ክፍት መደረጉ ይታወሳል፡፡ ፕሮጀክቱ በአካባቢው መልሶ የሚገነባውን የቀለበት መንገዱን ክፍል ጨምሮ 1.7 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና እስከ 46 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት አለው ፡፡ አሁን ላይ የሁለተኛው የተሸጋጋሪ ድልድይ ምሶሶዎች የማቆም ስራ በመገባደድ ላይ የሚገኝ ሲሆን በያዝነው በጀት ዓመት ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅ በተለይ በቦሌ ሚካኤል እና በሩዋንዳ አካባቢዎች ያለውን ትራፊክ መጨናነቅበከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ የትራፊክ ፍሰቱን እንደሚያሳልጥ ይጠበቃል፡፡ መንገዱ በአጠቃላይ 5.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው “የቦሌ ሚካኤል አደባበይ የላይና ታች መንገድ – ቡልቡላ ካባ መግቢያ” ፕሮጀክት አካል ነው፡፡ አሰር ኮንስትራክሽን የግንባታ ስራውን ሲያከናውን፣ ሀይ ዌይ ኢንጂነርስ አማካሪ ድርጅት ደግሞ የግንባታ ቁጥጥርና ክትትል ስራውን እያከናወነ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአሁን ወቅት ለቡ እና ኢምፔሪያል አደባባይ ላይ ተሸጋጋሪ ድልድዮችን እያስገነባ በመሆኑ ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በከተማዋ የትራፊክ ፍሰት ላይ አይነተኛ መሻሻል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
30,659 Responses to “የቦሌ ሚካኤል ተሸጋጋሪ ድልድይ”