በከንቲባ ጽ/ቤት የተጠሪ ተቋማት ቅንጅትና ማስተባባሪያ ዳይሬክቶሬት ለባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ክትትልና ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽ/ ቤት የተጠሪ ተቋማት ቅንጅትና ማስተባባሪያ ዳይሬክቶሬት የባለሥልጣኑን የ2018 በጀት ዓመት የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎች ያሉበትን አፈፃፀም አስመልክቶ ክትትልና ድጋፍ አከናወነ፡፡
የክትትልና ድጋፍ ስራው ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከዕቅድ ዝግጅት ጀምሮ የተከናወኑ የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎችና የሚያከናውነውን የመንገድ መሰረተ – ልማት አፈፃፀም በመቃኘት በቀጣይ መሻሻል የሚገባቸውን ተግባራት በመለየት ድጋፍ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
የክትትልና ድጋፍ ኮሚቴው አባላት እንደገለፁት፤ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ባለድርሻ አካላትን ለይቶ በቅንጅት ለመስራት እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ተግባር መሆኑን ጠቁመው፤ የ90 ቀናት ዕቅድ አፈፃፀም የተሻለ መሆኑን አንስተውዋል፡፡
ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ተልዕኮው ባሻገር፤ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ማህበራዊ አገልግሎቶችና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ያከናወናቸው ተግባራት በጠንካራ ጎን የሚታዩ መሆኑን የድጋፍና ክትትል አባላቱ ተናግረዋል።
የተቋሙን አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች በጠንካራ የህዝብ ግንኙነት ሥራዎች ለማጀብ የተደረገው ጥረት እና የባለድርሻ አካላትና የሰራተኞች ውይይት መድረክ በየጊዜው መካሄዱ እንዲሁም የ”ወርቃማው ሰኞ” መርሃ-ግብር አፈፃፀም የሚበረታታ መሆኑን የክትትልና ድጋፍ ኮሚቴ አባላቱ ጨምረው ገልፀዋል።
በክትትልና ድጋፍ ላይ የተገኙት በባለሥልጣን መ/ቤቱ የተቋም ለውጥና ሲስተም ዲዛይን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ገብሬ፤ በየጊዜው የሚደረገው ድጋፍና ክትትል እንደተቋም የተገኙ ለውጦችን አጠናክሮ በማስቀጠልና የታዪ ክፍተቶችን በማሻሻል ለበለጠ ውጤታማነት ለመስራት የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
