+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

በመንገድ ሀብት እንክብካቤ ላይ ያተኮረ የህብረተሰብ ንቅናቄ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25 ቀን 2017 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች ማህበር ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን እና ልሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር “ከተማችንን እናፀዳለን፤ ጤናችንን እንጠብቃለን” በሚል መሪ ሐሳብ፤ በከተማዋ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ መንገዶችን ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲጠብቃቸው ተነሳሽነትን ለመፍጠር ያለመ የህብረተሰብ ንቅናቄ ስራ አከናውኗል፡፡

በዛሬው ዕለት መነሻውን መሀል መርካቶ የገበያ አዳራሽ አድርጎ፣ በሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ – ፒያሳ አድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ድረስ በዘለቀው የህብረተሰብ ንቅናቄ፤ የባለሥልጣኑ አመራሮችና ሠራተኞችን ጨምሮ፣ የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና አርቲስቶች እእንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡

በባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢያሱ ሰሎሞን በንቅናቄ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ “በከተማችን በከፍተኛ የህዝብና የመንግስት ሀብት ፈሶባቸው የተገነቡት የመንገድ መሠረተ ልማቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ የመላው የከተማችን ነዋሪዎች የጋራ ጥበቃና እንክብካቤ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

አቶ ኢያሱ አክለውም በከተማችን የሚገኙ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ አደረጃጀቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች ማህበርን መልካም ዓርዓያ በመከተል፣ በየአካባቢያቸው የሚገኘውን የመንገድ ሀብት በመንከባከብ እና በመጠበቅ፤ እንዲሁም ህገ ወጥ ድርጊቶችን በመከላከል ረገድ ቀጣይነት ያለው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች ማህበር ምክትል ሰብሳቢ አቶ አንዱ ዓለም ጌታቸው በበኩላቸው «የአዲስ ወክ ኤንድ ፌስት» ንቅናቄ ዓላማ ማህበሩ የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሰዎች በጎዳናዎች ላይ እየተራመዱ በእንቅስቃሴ ጤናቸውን እንዲጠብቁና በመንገድ ላይ የተጣሉ ቆሻሻን በማንሳት፤ ንፁህ የከተማ ገፅታን የመፍጠር እና የመንገድ ሀብትን የመጠበቅ ባህልን የማዳበር ዋና ዓላማ ያለው መሆኑን ገልፀዋል።

Comments are closed.