+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

በ90 ቀናት ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10 ቀን 2017ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ጀነራል ካውንስል አባላትና በየደረጃው የሚገኙ የሥራ መሪዎች በቀጣይ 90 ቀናት በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

የውይይት መነሻ ሰነድ ያቀረቡት የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የምህንድስና የቴክኒክ አማካሪ ኢንጅነር ገዛኸኝ እሸቱ እንደገለፁት፤ በከተማ ደረጃ ከሚከናወኑ 18 የንቅናቄ አጀንዳዎች መካከል ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ 11 ግቦችን በመውሰድ ተግባራቱ ከመደበኛ ሥራዎች ጎን ለጎን በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩ አብራርተዋል፡፡

ከሰኔ 5 እስከ ጳጉሜ 5 ባሉት 90 ቀናት ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የሚከናወኑት ተግባራት የአረንጓዴ አሻራ፣ የኑሮ ውድነት ማረጋጋት፣ የክረምት በጎፈቃድ ስራዎች፣ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ማጠናቀቅ እና ቀጣይነት ባላው መልኩ መንከባከብ፣ የስራ እድል ፈጠራን ማሳደግ፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና ጥራት ተጠናቀው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ማድረግ፣ የ2017 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ምዕራፍ እና የ2018 በጀት ዓመት የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎችን ማከናወን ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውን ኢንጅነር ገዛኸኝ ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም፤ በመስከረም ወር የሚከበሩ ታላላቅ ሀገራዊና አካባቢያዊ በዓላት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እበሚያስገኝ እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲከናወኑ በቂ ዝግጅት ማድረግ፣ የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ስራዎችን ማጠናከርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት የዘጠና ቀናት ዕቅዱ አካል መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሙህዲን ረሻድ በበኩላቸው፤ የከተማ አስተዳደሩ ባስቀመጠው ልዩ የንቅናቄ ስራ አቅጣጫ የታቀዱ ግቦች እንዲሳኩ አመራሩና ሰራተኛው በላቀ ዝግጁነት በቅንጅት ወደ ተግባር እንዲገቡ አሳስበዋል፡፡

Comments are closed.