የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 29 ቀን 2017 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ገላን ጉራ በሚገኘው ቁጥር 22 ተስፋ የምገባ ማዕከል፤ ለአቅመ ደካማ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብር አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የተቋም ለውጥ እና ድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል ዶሌቦ፤ በመርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ከተሰጠው መደበኛ ተልዕኮው በተጨማሪ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስኮች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ቀደም ሲልም፤ በገላን ጉራ አካባቢ ለልማት ተነሺዎች በተዘጋጀው መንደር የመቃረቢያ መንገድ እና የአውቶብስ ተርሚናል ገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉን የጠቁሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብሮች ላይ በተለያዩ ጊዜያት የመሳተፍ እድል በማግኘታችን ደስታ ይሰማናል ብለዋል።
አቶ ጀማል አያይዘውም፤ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የዘንድሮውን የገና በዓል ምክንያት በማደርግ ያዘጋጀው የማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብር በየጊዜው የሚያካሂደው ሰናይ ተግባር አካል በመሆኑን ጠቁመው፣ ወደፊትም የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና በበኩላቸው፤ የከተማ አስተዳደሩ በርካታ ሰው ተኮር ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ለካዛችስ የልማት ተነሽዎች በተመሰረተው መንደርም 22ኛውን ተስፋ የምገባ ማዕከል በማቋቋም ለአቅመ ደካማ ነዋሪዎች የማዕድ ማጋራት መርሀሃ-ግብር እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አቶ አለማየሁ አክለውም፤ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የከተማዋን የመንገድ ሽፋን ለማሳደግ እየሰራ ከሚገኘው ተግባር ባሻገር፤ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች ማዕድ በማጋራቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለአደረገው የበጎ ፍቃድ ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበው፤ ሌሎች ተቋማትም በመሰል የበጎ ፈቃድ ተግባራት በመሳተፍ የበኩላቸውን ድርሻእንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።