የተረጅነት አስተሳሰብን በማስወገድ በውስጥ አቅም ችግሮችን ለመፍታት መረባረብ እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አመራርና ሰራተኞች “ከተረጅነት አስተሳሰብ መላቀቅና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የባለሥልጣን መስሪያቤቱ የተቋም ለውጥና ድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል ዶሌቦ እንደገለፁት፤ በሀገሪቱ ስር ሰዶ ከቆየው የተረጅነት አስተሳሰብ በመላቀቅ፣ በውስጥ አቅም ችግሮቻችንን ለመፍታት፣ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ሀገሪቱ ያላትን ሰፊ አምራች የሰው ኃይልና ምቹ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለዕቅዱ ተፈፃሚነት የበኩሉን ገንቢ ሚና ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የመወያያ ሰነዱን ያቀረቡት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢያሱ ሰሎሞን በበኩላቸው፤ በየጊዜው የሚገጥሙ ተፈጥሯዊ ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት በውጭ እርዳታ ጥገኝነት ላይ የተመሰረተውን አስተሳሰብ ከመሰረቱ መቀየር እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው ተጨባጭ ማሳያዎችን በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡
በምግብ እራስን በመቻል ከተረጂነት ለመላቀቅ የሚደረገው ጥረት፤ ሀገራዊ የልማትና የሰብዓዊ ድጋፍ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በነፃነት ለመተግበር፣ ሀገራዊ የመቋቋም አቅምን ለመገንባትና የውጭ ጥገኝነትን ለማስቀረት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ያለው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ከእርዳታ ፍላጎት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ከመሆኑም ባሻገር፣ ተገማችነት የሌለውና ከጉዳት በኋላ ዘግይቶ የሚገኝ በመሆኑ፣ በዘላቂነት ከቀውስ ለመዳን የሚያግዝ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም ለአደጋ ስጋት የማይበገር እና በራስ አቅም፣ የራስን ገመና ለመሸፈን የሚያስችል የተቀናጀ የልማት ስልት ገቢራዊ ማድረግ፣ የህልውናና የሉዓላዊነት ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ አቶ ኢያሱ ጠቁመዋል፡፡
በሁሉም መድረኮች ላይ የተካፈሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያያት፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የታለመውን ዕቅድ ተፈፃሚ ለማድረግ በሁሉም የሀገሪቷ ክፍሎች ሰላም ማስፈን፣ ልዩነቶችን በውይይት መፍታትና በቅንጀት መስራት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/
ዩቱዩብ:- https://www.youtube.com/@addisababacityroadsauthori1369