የድልድዮች ጽዳትና ጥገና ስራ እየተከናወነ ነው
መስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ለረጅም ጊዜ አገልግሎት በመስጠትና በተለያዩ ምክንያቶች ለከባድ ብልሽት የተዳረጉ ድልድዮችን እየጠገነ ነው፡፡
የወንዞችን ተፈጥሯዊ ፍሰት በማስተጓጎል ለድልድዮች ብልሽት ምክንያት እየሆኑ የሚገኙ የቆሻሻና የግንባታ ተረፈ-ምርት ክምችቶችን በማፅዳት እያስተካከለም ይገኛል፡፡
ባለስልጣኑ በዕቅድ ከያዛቸው ዘርፈ ብዙ የመንገድ መሰረተ ልማት ጥገና ስራዎች መካከል የድልድዮች ጥገና እና የጽዳት ስራ ይገኝበታል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የድልድይ ፅዳትና ጥገና ስራ ከተከናወነባቸው አካባቢዎች መካከል በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የአባ ጃሌ ድልድይ አንዱ ሲሆን፣ ድልድዩ ለረጅም ጊዜያት አገልግሎት ሲሰጥ በመቆየቱ ምክንያት እና በድልድዩ አካባቢ በሚጣል ቆሻሻና የግንባታ ተረፈ ምርት ሳቢያ የድልድዩ ምሰሶ ለጉዳት ተጋልጧል፡፡
አሁን ላይ በድልድዩ ሥር የተከማቸውና የወንዙን ፍሰት ያስተጓጎለውን ቆሻሻ በማንሳትና የድልድይ ጥገና ሥራ በማከናወን የነበረውን ችግር መፍታት ተችሏል፡፡
በተመሳሳይም በቦሌ ክፍለ ከተማ፣ በተለምዶ ፍየል ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ድልድይ ከፍተኛ መጠን ባለው ደለል እና ቆሻሻ በመደፈኑ ምክንያት የወንዙ ውሃ ወደ አስፋልት በመፍሰስ ለእግረኛ እና ተሽከርካሪ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ ሆኖ ከመቆየቱም በተጨማሪ በንብረት ላይም ጉዳት አድርሷል፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ወንዙ መስመሩን ጠብቆ እንዲፈስ ለማስቻል በድልድዩ ስር የተከማቸውን ከፍተኛ መጠን ያለው ቆሻሻና ደለል የማንሳት ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡
ሕብረተሰቡም የዝናብ ወቅት የጐርፍ አደጋ ምክንያት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለማስቀረትን እና በመንገድ ሀብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል፣ በየአካባቢው በመንገድ ዳር የውሃ መፋሰሻ መስመሮች እና ወንዞች ውስጥ ቆሻሻና የግንባታ ተረፈ ምርት የሚደፉ አካላትን በመከላከል በኩል የድርሻውን እንዲወጣ ባለሥልጣኑ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/
