የከተማዋ ወጣቶች በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5 ቀን 2015 ዓ.ም፡- ” ኢትዮጵያ የትዉልዶች ድምር” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ የሚገኘውን የትውልድ ቀን ምክንያት በማድረግ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ 150 ወጣቶች በከተማዋ በግንባታ ላይ የሚገኙ የተለያዩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በዛሬው ዕለት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
በመንገድ ጉብኝቱ ላይ ለወጣቶቹ ገለፃ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ሰሎሞን በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የህብረተሰቡን የመንገድ መሠረተ-ልማት ጥያቄ የሚመልሱ እና የከተማዋን ገፅታ እየቀየሩ የሚገኙ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ለመፍታት 6 የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድዮች በከፍተኛ መዋለ ነዋይ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች እየተገነቡ መሆናቸውን አቶ ኢያሱ ለጉብኝቱ ተሣታፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ኢያሱ አያይዘውም በመንገድ ሀብት አጠቃቀም ችግር ሳቢያ በከፍተኛ ወጪ የሚገነቡ መንገዶች ረጅም ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጡ እየተበላሹ እንደሚገኙ ገልፀው፤ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር የበኩላቸውን አውንታዊ ሚና እንዲወጡ ለወጣቶቹ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የከተማዋን የመንገድ ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፣ የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የመዲናዋን የትራፊክ ፍሰት ከማሳለጥ ባሻገር ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት የሚያላብሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በወጣቶቹ ከተጎበኙ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል የለቡ፣ የኢምፔሪያል እና የቦሌ ሚካኤል የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድዮች፣ የቃሊቲ-ቱሉዲምቱ እና የቃሊቲ አደባባይ – ቡልቡላ – ቂሊጦ እኔዲሁም የቦሌ ኤርፖርት – ጎሮ የመንገድ ፕሮጀክቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/
