+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ከጃፓን መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ የመንገድ ጥገና ማሽነሪዎች ርክክብ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 4 ቀን 2015ዓ.ም፡- ለአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ጥገና አገልግሎት እንዲውሉ ከጃፓን መንግስት በተገኘ ከ360 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ 79 ማሽነሪዎች የርክክብ ስነ-ስርዓት በዛሬው ዕለት ተከናወኗል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤን ጨምሮ ሌሎች የከተማዋ ከፍተኛ ኃላፊዎችና የባለስልጣኑ አመራሮች በተገኙበት የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል፡፡

በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የጃፓን መንግስትና ህዝብ ከኢትዮጵያ ጋር ለረጅም ዘመናት የዘለቀ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ጠቁመው፤ በእነዚህ ጊዜያት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚያጠናክሩ ትብብሮች መደረጋቸውን አውስተዋል።

በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ በኩል የተገኘው ማሽነሪዎች ድጋፍ በከተማዋ ውስጥ የተሻለ የመንገድ ጥገና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝና የትራፊክ እንቅስቃሴውን የተሳለጠ ለማድረግ አስተዋፆኦው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አያይዘውም የጃፓን መንግስት በተለያዩ ዘርፎች እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ወደፊትም ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸውንገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሚስስ ታኮ ኢቶ በበኩላቸው ዛሬ የተደረገው የጥገና ማሽነሪዎች ድጋፍ በመዲናዋ እያደገ ያለውን የመንገድ ሽፋን በዘመናዊ የመንገድ ጥገና እና አስተዳደር ስርዓት አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል እና የትራፊክ ፍሰቱን የተሳለጠ ለማድረግ ካለው አስተዋፆኦ ባሻገር፣ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትስስር ለማሳደግ እንደሚራዳ ጠቅሰው ፤ የጃፓን መንግስት በሁሉም ዘርፍ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ከፍተኛ ተወካይ ዶክተር ካታሱኪ ሞሮህራ፤ በጃፓን ሕዝብ በኩል የተረደገውን ድጋፍ አስመልክቶ እንደተናገሩት መንግስት ለመንገድ ልማት ዘርፉ በሰጠው ትኩረት የከተማው የመንገድ ኔትወርክ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን አስታውሰው የተደረገው ድጋፍ እያደገ ለመጣው የመንገድ ኔትወርክ ጥገና እና አስተዳደር ስራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡

የመንገድ ጥገና ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎችን የተረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ ባደረጉት ንግግር፤ የጃፓን መንግስት በትምህርት እና በቴክኖሎጂ የሚያደርገው ድጋፍ የተሻለ የመንገድ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እገዛን እያበረከተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ኢንጂነር ሞገስ አያይዘውም የከተማው የመንገድ ኔትወርክ እያደገ መምጣቱን ገልፀው ካደገው የከተማው መንገድ ሽፋን አኳያ ሰፊ የመንገድ ጥገና ስራዎች ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዛሬው እለትም በጃፓን ህዝብ በኩል የተደረገው ድጋፍ የመንገድ ጥገና አስተዳደር ስራውን በቀጣይ በማዘመንና አቅም በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ማሽነሪዎች በቀጣይ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ የከተማዋን የመንገድ ጥገና ስራዎች በስፋትና በጥራት የመፈፀም አቅምን ለማሳደግ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ሲሆኑ በዚህ ዙር ርክክብ ከተደረገባቸው መካከል ዳም ትራኮች፣ አስፋልት መቁረጫዎች፣ ኮምፓክተሮች ፣ክሬኖች፣ አስፋልት ሚክሰሮች ኤር ኮምፕረሰሮች፣ የድሬኔጅ ማፅጃ ተሽከርካሪዎች፣ ሎደሮችና ሌሎችም በርካታ ማሽነሪዎች ይገኙበታል ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.