የበጎነትን ቀን ምክንያት በማድረግ የህፃናት ድጋፍና ደም ልገሳ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 3 ቀን 2015 ዓ.ም፡- “በጎነት ለሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ በሚገኘው የበጎነት ቀን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አመራርና ሠራተኞች የደም ልገሳ እና በቋሚነት ለሚደግፋቸው 50 ህፃናት የአዲስ ዓመት በዓል መዋያ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሠራተኞች ለችግር ለተጋለጡ ሃምሳ ህፃናት በየወሩ በቋሚነት ከደመወዛቸው በማዋጣት ከሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ከባለስልጣኑ ሰራተኞች እና ከባለድርሻ አካላት በተሰበሰበ ገንዘብ የ2016ዓ.ም አዲስ ዓመት በዓል መዋያ ለእያንዳንዳቸው 2,000 ብር፣ 5 ኪሎ ግራም ዱቄት እና 5 ሊትር ዘይት ድጋፍ ተደርጓል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በመርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የባለሥልጣን መስሪያቤቱ አመራርና ሠራተኞች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ያደረጉት አርዓያነት ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ የበጎነት ተግባር ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም፤ የባስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለድርሻ አካላት ለሚቀርብላቸው የበጎ አድራጎት ድጋፍ ጥሪ ምላሽ በመስጠት እያበረከቱት ላለው አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በመሆን በህፃናት ድጋፍ እገዛ ለተሳተፉ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በዝግጅቱ ላይ የምስጋና ምስክር ወረቅት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለህፃናቱ በየወሩ ከሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ በ2015 በጀት ዓመት 850,600 ብር ግምት ያላቸው የምግብ ቁሳቁሶች ድጋፍ እና በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሀ ግብር የቤት እድሳት የሚያስፈልጋቸውን ህፃናት በመለየት የቤት እድሳት እንዲጀመርላቸው አድርጓል፡፡
የባለሥልጣኑ አመራር እና ሰራተኞች በዕለቱ ከህፃናት ድጋፍ በተጨማሪ የደም ልገሳ አድርገዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/
