የባለስልጣኑ አመራሮችና ሠራተኞች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት አካሄዱ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አመራርና ሠራተኞች ጳጉሜ 1 ቀን የሚከበረውን የአገልጋይነት ቀን ምክንያት በማድረግ “ሀገሬን መቼም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ አገለግላለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት አካሂደዋል፡፡
በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተቋም ለውጥና ሲስተም ዲዛይን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ አበዜ ሱሌማን ለፓናል ውይይቱ የተዘጋጀውን የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፤ በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የሚታዩ ጉድለቶችን በማረም በአዲሱ ዓመት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ሁሉም አመራርና ሠራተኛ መዘጋጀት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የፓናል ውይይቱን የመሩት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢያሱ ሰሎሞን በበኩላቸው፤ አገልጋይነት የህሊና እርካታን የሚያጎናፅፍ፣ የመልካም ስብዕና መገለጫ መሆኑን በመጥቀስ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት፣ ችግሮቹ የሚፈቱበትን ስልት በመቀየስና የተሻለ የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት የተገልጋዩን እርካታ ማሳደግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ዋነኛ ተዋንያን የሆኑት አገልግሎት ሰጪው እና አገልግሎት ተቀባዩ የሥነ-ምግባር መርሆዎችን አክብረው የአገልግሎት ልውውጥ ማድረጋቸው ከሙስናና አድሎአዊ አሠራር የፀዳ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ፣ ተገልጋዮችም ባልተገባ መንገድ አገልግሎት ለማግኘት ባለመሞከር የድርሻቸውን ገንቢ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ አቶ ኢያሱ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
የውይይቱ ተሣታፊዎች በበኩላቸው ህብረተሰቡ መብትና ግዴታዎቹን በሚገባ ተገንዝቦ በተገቢው መንገድ አገልግሎት ለማግኘት መታገል እንዳለበትና ሥራን በማጓተት ተገልጋይን የሚያንገላቱ አገልግሎት ሰጪዎችን በማጋለጥ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የህዝብ አገልጋይ የሆነው ፐብሊክ ሰርቪሱ የሥነ-ምግባር መርሆዎችን አክብሮ በመስራት የህብረተሰቡን እርካታ ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባት የጠቆሙት የውይይቱ ተሳታፊዎች፣ በአዲሱ ዓመት የመንግስት የሥራ መመሪያዎችን ማዕከል በማድረግ በቅንነት አገልግሎት በመስጠት የህብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/
