+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ቤት ለእምቦሳ፤ እምቦሳ እሰሩ

አንድ ሰው አዲስ ቤት ሰርቶ ሲያስመርቅ ወዳጅ ዘመዱ ሁሉ ባለቤቱን “ቤት ለእምቦሳ” በማለት ደስታቸውን የመጋራት ጠንካራ ባህል አለን፡፡

የቤቱ ባለቤትም “እምቦሳ እሰሩ” እያለ አፃፋውን ይመልሳል፡፡ የአባባሉ ትርጉም በደምሳሳው ሲታይ እንኳን ደስ አለህ፤ በአዲሱ ቤትህ እንቦሳ ጥጃ ተወልዶ ይፈንጭበት እንደማለት ይቆጠራል፡፡

ታዲያ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ሰላም ጎዳና አካባቢ አቅም ለሌላቸው የከተማዋ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖሪያ የሚሆን አንድ ባለ ሦስት ወለል ህንፃ በራሱ አቅም ገንብቶ ቤት ለእንቦሳ ብሏቸዋል፡፡

የመኖሪያ ህንፃው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ፣ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች የከተማዋ ኃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ ለአቅመ ደካማ ነዋሪዎቹ ከሌሎች የገና በዓል ስጦታዎች ጋር ተበርክቶላቸዋል፡፡

ይህ ህንፃ 21 የሚሆኑ ባለ አንድ መኝታ የመኖሪያ ቤቶች እና ለንግድ ስራ የሚሆኑ 3 ክፍሎችን የያዘ ነው፡፡

የመኖሪያ ህንፃውን በቦታው ተገኝተው በይፋ ያስመረቁት ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ከወሎ ሰፈር አደባባይ እስከ ኡራኤል ቤተክርስቲያን ድረስ ውብ የሆነ መንገድ ተሰርቶ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ አቅመ ደካማ ሰዎች በተጎሳቆለ ኑሮ እንዲኖሩ መፍቀድ የአብሮ የሚሄድ አይደለምና የሰዎችን ኑሮ መቀየር መቻል ትልቅ እርካታ የሚሰጥ በመሆኑ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራርና ሰራተኞች ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

እድሉ የደረሳቸው ነዋሪዎችም ከደስታቸው ብዛት ዳግም እንደተወለድን እንቆጥረዋልን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የቤት ባለቤት ከሆኑ የከተማዋ ነዋሪ ውስጥ ወ/ሮ ፋንቱ ወልድትንሳኤ አንዷ ናቸው እድሜ ባደከመ ጉልበታቸው ፈራርስ ልትወድቅ በደረሰች ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ኑሯቸውን ለመግፋት እጣ ፈንታቸው እንደነበር በምሬት ያስታውሳሉ፡፡ ዛሬ ይህን የመሰለ ዘመናዊ ቤት ባለቤት በመሆናቸው ደስታቸውን ለመግለፅ እንደተቸገሩ ይገልፃሉ፡፡

ወ/ሮ ብርሂት አምሳሉ በበኩላቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በተጎሳቆለ ቤት ውስጥ ከልጆቻቸው ጋር ኑራቸውን ሲገፉ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ አሁን ላይ የዚህ እድል ተካፋይ በመሆናቸው የተሰማቸው ከፍተኛ ደስታ ዳግም የተወለዱ ያህል ገልጸዋል፡፡ እኛም ቤት ለእምቦሳ ብለናቸው የደስታቸው ተካፋይ በመሆናችን የእነርሱን ከፍተኛ ደስታ በበአሉ ዋዜማ በመልካም ስራ ውስጥ አብረን ተጋራን፡፡

መልካምነት ለራስ ነው፤ መልሶ ይከፍላልና! መልካም ቀን!!

Comments are closed.